እኔ ምን አልኩና
ቤትሽ እየመጡ፣ መንገድ እያስቆሙ… ስለ አብሮነታችን - ለጠየቁሽ ሁሉ፣ እንደዚህ አልሽ አሉ፡፡ “ስለ እኛ አታንሱ፣ የሱን አታስታውሱ ! እኔማ ልጅት ሞኝ - ለፍቅር እኮ ስል፣ ቲማቲም መስዬ - ኳ ብዬ እስክበስል… እንደቡሄ ዳቦ… እሳት ነድዶብኛል - ከታችና ከላይ፣ እናሳ ምን ልሁን - እስቲ ከዚህ በላይ ?!” ማለትሽን ሰማሁ - አይደበቅ ወሬ፣ እርግጥ ውነትሽን ነው - አልዋሸሽም ፍቅሬ፡፡ ግንስ ከላይ ከታች - ያለው የእሳት ጠል፣ ወደ ውስጡ ዘልቆ - ዳቦ እንዳይቃጠል፣ ይለብስ የለም ወይ - ሙሉ የኮባ ቅጠል ? ታዲያ እኔስ ብሆን - አንቺ እንዳትጎጂ፣ ኮባሽ እንደነበርኩ - ተናገሪ እንጂ፡፡ እናም ለፍቅራችን - መስዋዕት መሆንሽ - በከንቱ አያስመካሽ፣ እኔ ተቃጥዬ - አርሬ እኮ ነው - እሳቱ የነካሽ፡፡ እንደውም ፍቅሬ ሆይ - አንቺ ታድለሻል፣ ገማጭ እንዳታጪ - በልኩ በስለሻል፡፡ እኔ ኮባሽማ - ልውል ስለማልችል ካንድ ጊዜ በላይ - ለድፎ ጋገራ፣ ካንቺ ላይ ተልጬ - ተጥዬልሻለሁ ከቆሻሻ ጋራ፡፡
*ገጣሚ ሲሳይ ታደሰ (ዘ-ለገሐሬ)









