ትውውቅ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጋር
አባታችን አዳም በሀጥያት ወድቆ ለሰው ልጆች በሙሉ የጻጋ ጉድለትን ሲያመጣ፤ የእርሱ እና የእኛ አምላክ እግዚአብሔር የሰው ልጅን በደረሰበት የጸጋ መጉደል ሊተወው አልፈቀደም። ይልቅ ሊያድነን ከሁሉ አስቀድሞ መረጠ ለእኛም የመዳናችንን ሚስጥር ሲናገር የሴቲቱ ዘር የእባቡን ራስ እንደሚቀጠቅጥ ጠቆመ(ዘፍ 3፡15 )። ይህ እስኪሆን እግዚአብሔር የሰው ልጅን ለአፍታ እንኳን ተለይቶት አያውቅም የአዳም ልጆችን ከክፋታቸው እየጠበቃቸው ከመካከላቸው ጻድቃንን እየመረጠ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳኑን ያፀና ነበር።
አብርሃምንም መረጠው “የምድርንም አህዛብ የሚያስባርከውን ቃልኪዳኑን[ዘፍ 12፡3፣ 22፡18]” ከእርሱና ከዘሩ ጋር አፀና፣ ቃልኪዳኑም ለይስሀቅ ከይስሀቅም ለእስራኤልና ለልጆቹ ሆነ። በእስራኤላውያንም አርጎ ራሱን ለዐለም ይገልጥ ነበር፤ እርሱ ምን አይነት አምላክ እንደሆነ፣ አለምን እንደሚያድን ዘላለማዊ ጌታም ከእነርሱ እንደሚያስነሳ ይገልጥላቸው ነበር። ይህም ዘላለማዊ ጌታ ኋላ ላይ የሚመጣው እራሱ እግዚአብሔር የሆነው የእግዚአብሔር የባህሪ ልጁ ክርስቶስ እየሱስ ነው። እርሱ በመጣ ጊዜ ከምድራዊ መንግስት የበለጠ ሰማያዊ የሆነውን የእግዚአብሔርን መንግስት በምድር ላይ አቋቋመ፤ ለሰው ልጅም የተገፈፈውን የእግዚአብሔርን ጸጋ መልሶ አለበሰው። ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜም ኪዳኑን አጸና ያቺም ኪዳን ከእርሷ በፊት የነበሩትን ኪዳናት ሽረት ሳትሆን ፍጻሜ ሆና አዲስ ኪዳን ተባለች። በክርስቶስም አምነው ከእርሱ ጋር አንድ በመሆን ለተባበሩት ተሰጠች። ይህ የክርስቶስ ና የምዕመኑ ህብረት ክርስቶስ የመሰረታት ቤተክርስትያን ተባላለች። ክርስቶስና እርሱ የላካቸው ሐዋርያቱ ስለቤተክርስትያን ካስተማሩት አንጻር ቤተክርስትያን የሚከተለውን ትመስላለች፡ “አንተ ዐለት ነህ በዚያችም አለት ላይ ቤተክርስትያኔን እሰራታለሁ” ብሏልና አንድ ቤተክርስትያን ናት “የሲዖልም በሮች አይበረቱባትም” ብሏልና የምጠፋ አይደለችም። አንድና የማጠፋ በመሆኗ ደግሞ ክርስቶስ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ የማጠፋ አንድ የሆነች ቤተክርስትያን ልትኖር ይገባል፤ ይህ እውነታ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ “እኔም እስከ ዐለም ፍጻሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ” ሲል በሰጠው ቃልኪዳን የተረጋገጠ ነው። ምንም እንኳን ሐዋርያቱ በዘመኑ ሁሉ ከእኛ ጋር በምድር ባይሆኑም፤ ስራቸው የሆነችው እነርሱ ያነጿት ቤተክርስትያን ግን አሁንም ድረስ ያለች ናትና ክርስቶስ ከጥንት ጀምሮ ያልተለያት ወደፊትም አብሯት የሚኖር ቤተክርስትያን ብቻ የእርሱ እውነተኛ ቤተክርስትያን ናት። በተጨማሪም መሪዎቿ እና ካህናቷ በምድርም ሆነ በሰማይ የማሰርና የምፍታት ስልጣን ያላቸው በመናፍስተና በደዌያትም ላይ ስልጣን ያላቸው እንዲሁም በምዕመኑም ላይ እንኳን ስልጣን ያላቸው ናቸው[ማቴ 16፡18-10 ፤ ሉቃስ 10 ፤ ማቴ 18፡17-18]። በአጭሩ ቤተክርስትያን የማይታይ መንፈሳዊ ህብረት ሳትሆን ከክርስቶስ ጀምሮ እስካሁን ያለች ፣ ሹማምንቶቿ(ካህናት) ስልጣን ያላቸው ፣ አንድ የሆነች፣ በአንዷም በእርሷ ምዕምኑ ሚመራበት ራሷ ክርስቶስ የሆነ የምዕመናን ህብረት ናት። ይህን ሁሉ የሆነችውን ይህችን ቤተክርስትያን በአሁኑ ጊዜ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እንላታለን።
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሐዋርያዊ መተካካትን/ቅብብሎሽን የተከተለ አማናዊ ክህነት ያላት፤ የኒቅያን ሃይማኖት እና ትምህርተ ተዋህዶን አጥብቃ የያዘች፣ ከለዳዊ(ካልቄዶናው) ያልሆነች ኦርቶዶክስ የሆኑ አብያተክርስትያናት ህብረት ናት። እነዚህ አብያተክርስትያናት
የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን፣ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፣የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን፣ የአርመንያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን፣ የአንጾክያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን፣ የህንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን
እነዚህ አብያተክርስትያናት አንዱ ሀይማኖት ላይ የተመሰረተ የተለያየ አይነት የአምልኮ ስርዐት አላቸው የኢትዮጵያ፣ የግብፅ ፣ የሶርያ እና የአርመንያ አብያተክርስትያናት የየራሳቸው አምልኮ ስርዐት(rite) አላቸው። እንዲሁም በአንዱ ሐዋርያዊ እምነት ላይ የተመሰረተ የተለያዩ ቀኖናዊ ስርዐቶሽ አሏቸው። የካልቄዶንንም ጉባኤ እንደተቀበሉ ከለዳውያን[ምስራቅ ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ ተሃድሷውያን] እርስበርሳቸው ሳይከፋፈሉ አንድ ሆነው የቆዩ ናቸው። በእነዚህ እህት አብያተ ክርስትያናት ውስጥ እና መካከል የሚፈጠሩት አለመግባባቶቸም መወጋገዝን ያላመጡ በዶግማ/ትምህርት ሳይሆን በክብር ወይም በፖለቲካ ጉዳይ የሆኑ ናቸው። ከተወሰኑትም በስተቀር አብዛኞቹ ተፈተዋል። ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ስሟ ሲጠራ ሁሌ አብሯት የሚጠራው የተዋህዶ አስተምህሮዋ ነው። ተዋህዶ፡ በራሱ ሙሉ የሆነ ከዊነ ወልድ ከድንግል ማርያም ከተነሳ ሰብዐዊ ከዊን ጋር በመዋሃድ አንድ ከዊን ከዊነ ስግው ቃል እንደተመሰረተ ሚያምን ትምህርት ነው። ሰብዐዊው ከዊን በውስጡ የራሱ ሌላ ማንነት ሳይሆን የእግዚአብሔር ወልድ ማንነትን የያዘ ነው። ቃልም ስጋ ከሆነ በኋላ ሰብዐዊ እና መለኮታዊ ንብረቶቹ ያለ መለያየት፣ መለዋወጥ፣ መቀላቀል እና መጠፋፋት በአንዱ ውህድ ከዊን፣ ባህሪ፣ ማንነት፣ ጌታ ውስጥ ያሉ ናቸው። ወልድም ያደረገውን በሙሉ ያደረገው እንደስግው ቃልነቱ እንጂ አንዴ እንደ ሰው ሌላ ጊዜ ደግሞ እንደአምላክ አይደለም። ክርስቶስም በመለኮቱ ከአብ ጋር በስብዕናው ደግሞ ከእኛ ጋር አንድ ነበር። በስብዕናውም ፍጹም ሰው ነበር ስጋውን ደግሞ ከድንግል ማርያም ነው የነሳው። እንደ ተዋህዶ አስተምሮ እንደየዐውዱ ስለሁለትም/ አንድም ፈቃድ መናገር የተለመደ ተግባር ነው። ፈቃድ ፍላጎትን የሚያመልክት ከሆነ ልክ እኛ ስጋዊና መንፈሳዊ ፍላጎት እንዳለን፤ክርስቶስም ሰብዐዊና መለኮታዊ አለው። ፈቃድ ግን ውሳኔን ከሆነ ሚያሳየው ወይም ለተግባር ከሆነ ሚውለው በዚህ መልኩ ክርስቶስ አንድ ፈቃድ ብቻ ነው ያለው።
ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ሶስት አለማቀፍ ጉባኤያት አሏት፡ የክርስቶስን የባህሪ አምላክነት የካደው አርዮስ የተወገዘበት የኒቅያ ጉባኤ[325]፣ የመንፈስ ቅዱስን አምላክነት የካደው መቅዶንዮስ እና ክርስቶስ ነብስንም ጭምር ንብረቱ ማድረጉን የካደው አቡሊናርዮስ በአንድ ላይ የተወገዙበት የቁስጥንጥንያ ጉባኤ[381] እንዲሁም የድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክነትን ክዶ ክርስቶስን ለሁለት የከፈለው ንስጥሮስ የተወገዘበት የኤፌሶን ጉባኤ[431] ናቸው። በእነዚህ ጉባኤያት የወጡት የተረቀቁት መግለጫዎች በሙሉ ከጥንት ጀምሮ የነበረውን የሃይማኖቱን እውነታ ሚገልፁ ናቸው። ዐለም አቀፍ አይሁኑ እንጂ በአሌክሳንድርያው ዲዮስቆሮስ የተመራው ሁለተኛ የኤፌሶን ጉባኤ[449] እና በአሌክሳንድርያው ጢሞቴዎስ የተመራው ሶስተኛ የኤፌሶን ጉባኤም[475] በቤተክርስትያናችን ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው። ከዛ በተረፈ ግን ከለዳውያን የሚቀበሏቸውን ሌሎች ዐለም ዓቀፍ ጉባኤያት በተለይ የካልቄዶን ጉባኤን[451] አንቀበልም። በካልቄዶን ጉባኤ የዲዮፊትዝም[ክልዔ ባህሪ] ትምህርት ተቀባይነት ስላገኘ ፣ ክርስቶስን ልክ እንደ ንስጥሮስ ለሁለት በመክፈሉ በ ሁለተኛ የኤፌሶን ጉባኤ የተወገዘው ቴዎዶሬት ተመልሶ ስለጸደቀ፣ እንዲሁም ክርስቶስ በሁለት ባህሪያት አለ የሚለው የሌዮን ጦማር ስለጸደቀ አንቀበለውም።
ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ዲዮፊቲዝምንም[ክልዔ ባህሪ] ሆነ ሞኖፊቲዝምንም አትቀበለም፡ ምንም እንኳን አንዳንዴ በአላዋቂዎች እርሷ እራሷ ሞኖፊሳይት ናት እየተባለች ብትከሰስም፤ ቤተክርስትያን ግን የአውጣኪን ሞኖፊትዝም አትቀበለውም። የአውጣኪ ሞኖፊቲዝም የክርስቶስ ስብዕና በመለኮቱ ውስጥ እንደተዋጠ ስለሚያስተምር በሶስተኛው የኤፌሶን ጉባኤ ተወግዟል። የዲዮፊቲዝም አስተምህሮ ደግሞ በተሀድሷውን ዘንድ የንስጥሮስን አስተምህሮ ቅርጽ በግልፅ የያዘ የሚመስል፤ ቃል ስጋ ሳይሆን ቃል በስጋ አደረ አይነት ትምህርት ሲሆን፤ በሌሎች ከለዳውያን ዘንድ ደግሞ ክርስቶስ ከሁለት ከዊናት መሆኑን የሚቀበል ሳይሆን ሰብዐዊ ባህሪው ከዊን አልባ እንደሆነ የሚያስተምር ነው። ያም ይሁን ይሄ ልክ አይደሉም፤ በመሆኑም እኛ ምንቀበለው በመጀመሪያው የኤፌሶን አለም አቀፍ ጉባኤ ትምህርቱ የጸደቀው የቅዱስ ቂርሎስን የተዋህዶ[ሚያፊቲዝም] ትምህርት ብቻ ነው።
ቤተክርስትያን ከየትኛውም ከሌላ ህብረት በላይ መንፈሳዊነት ላይ ታተኩራለች በመሆኑም በቅዳሴያዊ ስርዐትና በገዳማዊ ስርዐት እጅግ የበለጸገች ከመሆኑም በላይ የገዳማዊ ስርዓትም ምንጭ ጭምር ናት። በቤተክርስትያን ውስጥ የተፃፉ አብዛኞቹ መጻፍት መንፈሳዊነት ላይ ያተኮሩ ናቸው። መፃፍቶቹ ብቻ ሳይሆኑ ደግሞ ስርዐቶችም ጭምር መንፈሳዊነት ላይ ያተኮሩ ስለሆኑ፡ እንደ አዋጅ አጿማት እና ጸሎታት ያሉ የተለያዩ ስርዐቶች አሉን። የእግዚአብሔር ቅዱስ ቤተመቅደስ የሆንን እኛ ምዕመና ከሀጥያት ርቀን የመንፈስ ቅዱስን ቤተመቅደስ እንዳናቆሽሽ እነዚህ አጿማት፣ ጸሎታት እና ስርዐቶች ታዘውልናል። እነዚህ ስርዐቶች እና የጾም ወቅቶች እንደየ እህት አብያተክርስትያናት አምልኮ ስርዐት ሊለያይ ቢችልም ዋና አላማቸው ግን የምዕመኑን መንፈሳዊ ተጋድሎ ማበርታት በመሆኑ አንድ ነው። በመንፈሳዊ ተጋድሏችንም ይረዱን ዘንድ ቤተክርስትያን ካህናትን የንስሐ አባት አርጋ ሰጥታናለች። በስነ መለኮት ትምህርቷም አይምሮን ብቻ ሳይሆን መንፈስንም ጭምር ልታረካ ስለምትሻ፤ ብዙ መንፈሳዊ የጥበብ ስራዎችን እና እንደነ ሶርያዊው ማርያዕቆብ ፣አርመንያዊው ጎርጎርዮስ ነርካጺ እና ኢትዮጵያዊው ያሬድ ዘአክሱምን ያሉ መንፈሳዊ ጠቢባንን አፍርታለች።
ሐዋርያዊት በመሆኗም የሐዋርያዊ እና አለማቀፍ ቤተክርስትያንን ትውፊት አጥብቃ ይዛለች፤ ህብረቷን እና ትምህርቷንም የምታመጣው ከዚው ትውፊት እንጂ ከሌላ እይደለም፤ እነዚህ ትውፊቶች በቅዱሳን መጻሀፍት፣ በሐዋርያት የቃል ትምህርቶች ፣ በቤተክርስትያም ቅዳሴ እና የአምልኮ ስነስርዐት እንዲሁም በጉባኤያቷ ውስጥ ይገኛሉ። ምዕመናን እነዚህን ትውፊቶች ሲኖሩና ሲያስተምሩ እግዚአብሔር በዛ ኑሯቸው ውስጥ ሃይማኖቱን በየጊዜው ይግልጣል በዚህ ትውፊት ውስጥ ከተገለጠውም ውጪ ሌላው ኦርቶዶክስ አስተምህሮ አይደለም። ይህ ቅዱስ ትውፊት እንደየጊዜውና እንደየቦታው ይዘቱን ሳይለቅ በተለያየና በተሻለ መልኩ ሊገለጽ ይችላል፤ ይህም የምዕመናኑን ወግ እና ስርዐት እንዲሁም በጊዜው ከነበረው ምንፍቅና አንጻር ሊሆን ይችላል።
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ራሷ ክርስቶስ የሆነ አንድ አካል፤ የሀዲስ ኪዳኑም ሕዝብ ናት። ከቤተክርስትያን ውጪ መሆን ከክርስቶስ ውጪ መሆን ስለሆነ ያለ ቤተክርስትያን ድህነት የለም፤ በኖህ መርከብም ትመሰላለች፤ ድህነትም ተሰጥቶ ሚተላለፈው በእርሷ በኩል ነው። ይህንንም ታደርግ ዘንድ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት እና ሌሎች ምዕመናን አሏት እኒህም በሜሮን ክርስትያን ሁሉ ወደሚሳተፍበት ወደ መንግስቱ ክህነት የተቆጠሩ ናቸው። ከእነርሱም አንዳንዱ ክርስቶስ ገልጦ ለሰጠው የመልከጼዴቅ ክህነት የተለዩ እና ቀሳውስት ፣ ኤጲስቆጳሳት ፣ ጳጳሳት ወዘተ እየተባሉ ሚጠሩ፤ የቤተክርስትያኑ ኃላፊዎች ናቸው። ክርስቶስ ለእነርሱ በሚሰጠው ስልጣን ተጠቅሞ እንደ ጥምቀት፣ ቁርባን ፣ ንስሀ ባሉት ሚስጥራት ምዕመኑን ከሀጥያት እያነፃ ይቀድሳል።
ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በውስጧ ያሉት ነዋየ ቅዱሳን እና ሚስጥራት ብዙና ጸጋን ለማስተባበር የሚውሉ ናቸው፤ መንፈስ በንዋየ ቅዱሳን እንደሚሰራ ታምናለችና ለስዕላት ተለቅ ያለ ቦታ አላት፤ በስዕላቷ ታሪኳን እንደየምዕመኑ ወግ[የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን በኢትዮጵያ የስዕል ጥበብ፣ የሶርያ በሶርያ፣ የአርመን በአርመን] ታስተምራለች የእግዚአብሔርንም ቤት ታስውባለች፤ በታሪኳም ከባድ የአይኮኖክላዝም ግጭት ገጥሟት አያቅም። ከአሏት ብዙ ሚስጥራት ውስጥ በዋናነት ሰባት ሚስጥራት ይጠቀሳሉ [ሚስጥረ ጥምቀት ፣ ሚስጥረ ሜሮን፣ሚስጥረ ቀንዲል ፣ ሚስጥረ ቁርባን ፣ሚስጥረ ጋብቻ ፣ሚስጥረ ክህነት እና ሚስጥረ ንስሀ] ከሌሎቹ ሚስጥራት በተለየ መልኩ በእነዚህ ድህነትን አግኝተን እንፈጽማለን። ሁሉም አማኝ ከእነዚህ ቢያንስ አራቱን ሊፈጽም ይገባል [ጥምቀት ፣ ሜሮን ፣ ቁርባን እና ንስሀ] ሚስጥረ ጥምቀት ከሚስጥራት ሁሉ የሚቀድም የሀጥያት ስርየትን የምናገኝበት ፣ በጸጋ ጉድለት የተጎዳው መንፈሳችን ሚታደስበት ፣ አዲስ ተፈጥሮ ምናገኝበት ፣ የእግዚአብሔርን ልጅነት የምናገኝበት እና ወደ ቤተክርስትያን ተቀላቅለን ከምትሰጠው ዘላለማዊ ህይወት ተካፋይ የምንሆንበት ሚስጥር ነው [1 ጴጥ 3፡21 ፣ የሐዋ 2፡38 ፣ ገላትያ 3፡26-27 ፣ ቲቶ 3፡5 ]። ልክ ሚስጥረ ጥምቀት እንደተፈጸመ ሚስጥረ ሜሮንም አብሮት ይፈጸማል፤ በዚህ ሚስጥር መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን አድሮ በጥምቀት የተቀበልናቸውን ነገሮች ሁሉ ይጸናሉ፤ መንፈስ ቅዱስም ጭምር በውስጣችን ይጸናል ፣ ስጦታውን እንቀበላለን ፣ ሰውነታችንም ይቀደሳል፣ በሜሮንም የእግዚአብሄር ቤት መቅረታችን ይጸናል [የሐዋ፡5-17 ፣ 1ዮሐ 2፡20]። በቤተ ክርስትያናችን ውስጥ ተጠምቆ የተቀባ ሰው ብቻ አማናዊ የጌታ ስጋና ደም የሆነውን ቁርባኑን ለመቀበል የቻላዋል። ይህች ትዕዛዝ ጌታ እራሱ በመጨረሻው እራት የሰጣትን ትዕዛዝ ተከትለን የምንፈጽመው ነው፤ በቤተክርስትያናችንም ውስጥ እውነተኛ ስጋና ደም እንደሆነ ይታመናል፤ ሚስጥሩም ታላቅ ነው ይህን የመረመሩ አብዛኞቹ አባቶች የምንመገበው ዳቦና ወይን ይዘቱ ሳይቀየር የስጋና ደሙ ይዘትንም እንደሚይዝ ሲያምኑ፤ የተወሰኑት አባቶች ደግሞ የዳቦውና ወይኑ ይዘት ጠፍቶ የስጋና ደሙን ይዘት እንደሚይዝ፤ ይህ የሚሆነው ደግሞ በዳቦና ወይን መልክ እንደሆነ ያምናሉ። በሁሉም ዘንድ ግን ቁርባን የጌታ እውነተኛ ስጋና ደም እንደሆነ ይታመናል። በአማኞች የመንፈሳዊ ተጋድሎ ኑሯቸው ውስጥ ለሚሰሩት ሃጥያት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲታደሱ ደግሞ ምስጢረ ንስሀን ይፈጽማሉ፤ በዚህ ሚስጥር ለምዕመኑ እግዚአብሔር ልክ በጥምቀት የሀጥያት ስርየትን እንዳደረገላቸው በካህናቱ አድርጎ የሀጥያት ስርየትን ይፈጽመላቸዋል። የዚህ ሁሉ ነገር አላማው በመንፈሳዊ ተጋድሎ እና ከእግዚአብሔር ጸጋ ጋር በመተባበር ድህነትን መቀበል ነው።
የቤተክርስትያን ነገረ ድህነተ አስተምህሮ፤ የእግዚአብሔር ስጦታን የመቀበል ህብረታዊ ህይወት ነው ማለት ይቻላል። እኛ ለምንሰራው መልካም ስራ የተከፈለን ዋጋ አይደለም፤ በሕጋዊ ስምምነት በአንድ ጊዜ የተሰጠን ማዕረግም አይደለም። እግዚአብሔር አስቀድሞ ገና አመፀኞች ሳለን ወዶናልና የእርሱን መውደድ ለማግኘት ብለን ማድረግ የሚጠበቅብን ምንም አይነት ተግባር የለም፤ እርሱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሰጠንን የመዳን ጸጋ ግን ፈቃዳችንን ከእርሱ ፈቃድ ጋር በማስተባበር መቀበል ይኖርብናል። የእኛ የመዳናችን ፍጻሜ የሚሆነው ከእግዚአብሔር ጋር አንድ[አማልክት ዘበጸጋ/deified] በመሆን ጌታ “በሰማይ ያለው አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ[ማቴ 5፡48] ” ያለውን ትዕዛዝ በመፈጸም ነው። ይህን ለማረግ በፍቅር የሚሰራ እምነት ያስፈልጋል፤ ምክያቱም ፍቅር እውነት የሚሆነው ነጻ ከሆነ ብቻ ነው፣ ነጻ ለመሆን ምርጫ እና መራጭ ያስፈልጋል፡ የኛ ምርጫ ደግሞ ሚሆነው በፍቅር ፈቃዳችንን ማስተባበር ነው። በእምነት በመኖር በየጊዜው እንጸድቃለን[ዘፍ 15፡6 ፣ ያዕ 2፡21-24]: በቅድሚያ በማመን አልያም በጥምቀት በሚደረግልን የሐጥያት ስርየት እንጸድቃለን ቀጥሎም በምንኖረው ኑሮ ፈቃዳችንን አስተባብረን ጸጋን በመቀበል እየጸደቅን እንቀደሳለን። ቤተክርስትያን ሰው በራሱ ዳነ ብላ አታስተምርም እንደውም እንደ እምነት እና ንስሀ ያሉ ንብረቶች የባህሪ ሳይሆኑ የጸጋ ናቸው እያለች የእግዚአብሔርን አዳኝነት ሁሌም ከፍ ታደርጋለች፤ ስጦታም ስለሆነ ተቀባይ እንደሚያስፈልገው ታስተምራለች። ይህ አይነቱ በፍቅር የሚሰራ እምነት በእግዚአብሔርና በሰው ህብረት[synergia] ብቻ እንደሚሆን፤ በዚህም መልኩ የአዲስ ኪዳን ህዝብ ድኖ ወደ ቀድሞው ክብር እንደሚመለስ በጽኑ ታስተምራለች።
ቤተክርስትያን ሰማያዊ መንግስት ናትና የዚህ አለም ገዢ ከጥንት ጀምሮ አሁንም ድረስ ጭቆና እና በደል ያደርስባታል። እስከ አራተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የሮማ መንግስታት ክርስትያኖችን በግፍ ሲገድሉና ሲያሰቃዩ ፣ በደማቸውም እንዲጠመቁ ሲያደርጉ ቆይተው እነርሱ ሲያርፉልን ደግሞ ከለዳውያን ቤተክርስትያንን ሊያጠፋ ቆርጠው ተነስተው ብዙ የግፍ ጭፍጨፋ ሲያደርሱብን ነበር። የግብፅ ቤተክርስትያን በአንድ ጊዜ 30,000 ምዕመን አጥታ ታቃለች፣ ከዚህም በኋላ በሙስሊም አረቦች አገዛዝ ስር ከብዝሀንነት ተርታ ወጥተዋል፡ አሁንም ድረስ በግብፅ ውስጥ ብዙ ስቃይ እየደረሰባቸው ይገኛል። አርመን ክርስትያኖች በፋርስ እና በሙስሊም መሪዎች ከፍተኛ የዘር ጭፍጨፋ ደርሶባቸዋል፤ በተለይ በቱርክ መንግስት ግማሽ በሚሆኑ አርመናውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ ደርሷል። የዛሬን አያርገውና ሶርያ ብዙሀኑ ክርስትያን ነበሩ፤ በቁጥራቸውም እጅግ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ በፍልስጤም ፣ ሜሶፖታሚያ ውስጥም ሳይቀር ምዕመናን ነበሯት፤ ከሙስሊም መሪዎች የጭቆና አመራር ስር ግን ይህ ሁሉ ቀርቷል። እስልምና ሳይመጣ በፊት ኑቢያ የክርስትያን ሀገር ነበረች፣ ጆርጂያ በፖለቲካል ጉዳይ ወገን ቀይራ ነው እንጂ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ነበረች። ባጠቃላይ ቤተክርስትያን በካልቄዶን ጉባዔ ጊዜ እስክ መጪዎቹ 200 አመታት ድረስ ከካልቄዶናውያን ያልተናነሰ ምዕመን ነበራት እስካሁን ድረስ ባላለቀ የሰማዕታት ዘመን ውስጥ በመኖሯ አሁን ያለችበት ላይ ደርሳለች[ቅዱስ አጥናቴዎስ እንዳለው “ለቤተክርስትያን ታማኝ የሆኑና ትውፊቷን የሚጠብቁ ቁጥራቸው እንኳን ቢቀንስ የክርስቶስ እውነትኛ ቤተክርስትያን እነርሱ ናቸው”]። እንደዚም ሆኖ አሁን ላይ ቤተክርስትያን በብዙ ቦታዎች እየተስፋፋች ሄዳለች፡ በጃፓን ፣ በፊሊጲንስ፣ በቦሊቭያ፣ በብራዚል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያናት ተመስርተዋል። በግዋታማላ ውስጥ ከ 700,000 በላይ የሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ምዕመናን አሉ፤ ሌሎች ደግሞ በፓኪስታን እና ኢንዶኔዥያ ውስጥ ይገኛሉ። በአሜርኪና በአንዳንድ የዐውሮፓ ሀገራት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይግኛል፤ ከዚህ በላይም እንደሚጨምር ይጠበቃል። ባጠቃላይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የድህነት ቤት የሆነች አንዷና እውነተኛዋ ቅድስት ፣ ኩላዊት ፣ ሐዋርያዊት ቤተክርስትያን ናት “ሁሉን በፈጠረ አንድ አምላክ በሆነ በአብ የምታምን ፤ ሰማይና ምድርን በፈጠረ የሚታየውና የማይታየው ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በጌታ በእየሱስ ክርስቶስ : 'ከብርሀን የተገኘ ብርሀን፣ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ እውነተኛ አምላክ፣ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ፣ በባህሪው ከአብ ጋር የሚተካከል፣ ሁሉ በእርሱ የሆነ፣ በሰማይም ካለው በምድርም ካለው ያለእርሱ የሆነ ምንም የሌለ፣ ስለእኛ ስለሰዎች እኛን ለማዳን ከሰማይ የወረደ፣ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ፍጹም ሰው የሆነ፣ ደግሞ ስለእኛ የተሰቀለ፣ በጴንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን መከራን ተቀብሎ ሞቶ የተቀበረ፣ በሶስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ የተነሳ፣ በቅዱሳንም መጻሀፍት እንደተጻፈው በክብር በምስጋና ወደሰማይ ያረገ፣ በአባቱም ቀኝ የተቀመጠ፣ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ላይ ለመፍረድ በምስጋና የሚመጣ፣ ለመንግስቱም ፍጻሜ የሌለው' ብላ የምታምን ፤ በመንፈስ ቅዱስም፡ 'እርሱ ጌታ ሕይወት የሚሰጥ፣ ከአብ የሰረፀ፣ ከአብ እና ከወልዳ ጋር በአንድነት የምንሰግድለትና የምናመሰግነው፣ በነቢያትም አድሮ የተናገረ ነው ' ብላ የምታምን ናት“
እግዚአብሔርም እስካሁን ከሐዋርያቱና ከቅዱሳኑ ጋር በህብረት በመሆን አንጿታል፤ ካሁን በኋላ ያለውን የማነጽ ስራ ደግሞ ከልጆችዋ ከምዕመናን ጋር የሚያደርገው ይሆናል። አሜን።












